የህይወት ትርጉም

ከፊታችሁ ተገኝቼ ንግግር እንዳቀርብ እድሉ ስለተሰጠኝ ከፍ ያለ ክብር ይሰማኛል:: እናም ማለት የምፈልገው ከፊታችሁ የቆምኩት እንደ አዋቂ ለማስተማር አይደለም:: እኔም እንደ አዋቂ ለማስተማር ዝግጁ ነኝ ብየ አላስብም:: ከዛ ይልቅስ የራሴን ምክር ልመክር ብል ይገልጸዋል:: ምክንያቱም ራሴን ከፊቴ ካሉት ወንበሮች አስቀምጬ አይዋለሁና ነው:: ከጥቂት ቀናት በፊት፣ ከጥቂት አመታት በፊት፣ ከጥቂት ጊዜያት በፊት _ እኔም እናንተ ካላችሁበት ወንበር ላይ ተቀምጬ ነበር፣ ከየትም ይምጣ _ የመጣበት ትርጉም የለውም:: ሰው ሆኖ ስለ እስልምና ግንዛቤ የሌለው:: እናም በዛች ቅጽበት፣ እኔም ያ ሰው ነበርኩ የህይወት ትርጉምን ምንም ያልተረዳና ያልገባው!

ስለዚህ በዚህ አስታዋሽነት፣ እያልኳችሁ ያለሁት እንደ አዋቂ ማስተማር ሳይሆን እንደ መረጃ እና እንደምክር እንድታስቡት ነው:: ላጋራችሁ ያሰብኩትም መረጃ ትንሽ ሰፋ ያለ ቢመስልም፣ የሰውን የአዕምሮ ልቀት፣ የማቀናበር ችሎታውና የማከማቸት አቅሙን ስታስቡት በእነዚህ ጥቂት ገጽ መረጃወች በእርግጥም እንደማያጨናንቃችሁ ልነግራችሁ እወዳለሁ::

በዛሬው እለትም የምንወያይባቸውን ነጥቦች ላሳውቃችሁ ኃላፊነት አለብኝ _ የህይወት ትርጉሙ ምንድን ነው? እናም ደግሞ የሚከተሉትን ይጠይቃል _ “ስለ እስልምና ምን ታውቃላችሁ” ማለት _ ስለ እውነት ስለ እስልምና ምን ታውቃላችሁ? ስለ እስልምና የሰማችሁትን አይደለም፤ ወይም ደግሞ አንዳንድ ሙስሊሞች ስለሚያደርጉት አይደለም፣ ግን ስለ እስልምና ምን እንደምታውቁ እንጂ?

ይህን እድል ስላገኘሁ ክብር ይሰማኛል፣ ሁላችሁም እኩል ኃላፊነት አለባችሁ ብየ ብጀምር ደስ ይለኛል:: እና ያ ኃላፊነት ማንበብ ወይም ማደመጥ ነው _ በንጹህ ልቦና እና በሚያገናዝብ አዕምሮ::

ባለማወቅ እና በባህል ተጽዕኖ በተሞላች አለም ውስጥ ከድርጊታቸው በፊት ላማሰብ ትንሽ ጊዜ የሚሰጡ ሰወችን ማግኘት ይበልጥ አስቸጋሪ ሆኗል:: ስለ ህይወት እውነታ ለማሰብ፣ የዚህችን አለም እውነት ለመድረስና የነፍሳችንን ዋጋ ለማወቅ፣ እንዳለመታደል ሆኖ ግን አብዛኛውን ሰው እጅግ መሰረታዊና ጠቃሚ የሆነውን ጥያቄ “የህይወት ትርጉሙ ምንድን ነው” ብላችሁ ስትጠይቁት በማየት እና ነገሮችን በመገምገም ምላሽ መስጠት የማይችሉ ናቸው:: በብዙ አጋጣሚዎችም፣ ሌላ የሆነ ሰው ሲል የሰሙትን ሊነግሯችሁ ይችላሉ ወይም የወል የጋራ የሆነ አስተሳሰብ ሲያንጸባርቁ ይስተዋላሉ::

አባቴ ስለህይወት ትርጉም እንደተናገረው፣ የቤተክርስቲያኒቱ ሚኒስቴር እንደተናገረው፣ የትምህርት ቤቴ መምህር እንደተናገረው፣ ጓደኛየ እንደተናገረው::

ማንንም የመብላትን ጥቅም ብጠይቀው፣ “ለምን እንመገባለን?” የአብዛኛው ሰው ምላሽ የሚሆነው ተመሳሳይ አንድ ምላሽ ነው፣ “ለስነ ምግብነቱ” ምክንያቱም ህይወትን የሚያስቀጥል ስለሆነ:: ማንንም ለምን ስራ እንደሚሰሩ ብጠይቃቸው፣ ምላሻቸው የራሳቸውንና የቤተሰቦቻቸውን ፍላጎት ለማሟላት የሚል ይሆናል:: ማንንም ለምን እንደሚተኙ፣ ለምን እንደሚታጠቡ፣ ለምን እንደሚለብሱ የመሳሰሉትን ነገሮች ብጠይቅ ምላሻቸው “ለሁሉም የሰው ልጆች መሰረታዊ ፍላጎት እንደሆነ ይነግሯችኋል” ይህን መሰል ብዙ መቶ ጥያቄዎችን ብንደጋግም ምላሹ ተመሳሳይ ይሆናል፣ በማንኛውም ቋንቋ፣ በማንኛውም ቦታ፣ በቀላሉ ለመግለጽ በየትኛውም የአለም ክፍል ተመሳሳይ መልስ:: ግን ለምን “የህይወት አላማና ትርጉሙ ምንድን ነው?” ብለን ስንጠይቅ የተለያየ መልስ የምናገኘው? ምክንያቱም ሰው ግራ ተጋብቷልና ነው፣ በትክክል ምን እንደሆነ አያውቁም:: በጨለማ ውስጥ ይዳክራሉ:: “አላውቀውም” ላለማለትም እንዲህ ነው ተብለው የተሞሉትን፣ መልስ ነው ብለው ይናገራሉ::

ስለዚህ ነገር ትንሽ እናስብ:: የኛ የመኖራችን ትርጉም እንዲሁ ለመብላት፣ ለመተኛት፣ ለመልበስ፣ ለመስራት፣ ሀብት ለማፍራት እና ለመደሰት ነው? በቃ ይህ ነው የኛ የመኖራችን ትርጉም? ለምን ተወለድን? የመኖራችን ትርጉም ምንድን ነው፣ አስገራሚ ከሆነው ሁለንታ እና ከስነ ፍጥረት በስተጀርባ ያለው ጥበብ ምንድን ነው? ስለጥያቄው በደንብ አስቡበት!

አንዳንዶች ስለ ፈጣሪ ህልውና ምንም ማረጋገጫ የለም ብለው ይከራከራሉ፣ ስለ አምላክ ማረጋገጫ የለም ይላሉ፣ ይህ ሁሉ ፍጥረት፣ ይህ ሁሉ ሁለንታ በፈጣሪ የተሰራ እንደሆነ ማረጋገጫ የለም ይላሉ:: እንዲህም ብለው የሚያምኑ አሉ : አለሙ ሁሉ እንዲሁ በአጋጣሚ የመጣ ነው:: በቢግ ባንግ መላው አለማት እንዲሁ ዝም ብሎ የመጣ የተገኘ ነው:: ህይወትም ይህ ነው የሚባል ሊገለጽ የሚችል ትርጉም የለውም በማለት ይከራከራሉ፣ ስለ አምላክ ስለ ህይወት ትርጉሙ ወይም ስለ አለሙ ፈጣሪ ማረጋገጫ በሳይንስም ሆነ በ ሎጂክ ሊያረጋግጥ የሚችል ምንም ነገር የለም::

እዚጋ ከቅዱስ ቁርዐን ስለዚህ ጉዳይ የሚገልጹ የተወሰኑ ቃላትን ልግለጽ::

“ሰማያትንና ምድርን በመፍጠር ሌሊትና ቀንም በመተካካት ለባለ አእምሮዎች በእርግጥ ምልክቶች አሉ (እነርሱም) እነዚያ ቆመው ተቀምጠውም በጎኖቻቸው ተጋድመውም አላህን የሚያወድሱ በሰማያትና በምድር አፈጣጠርም የሚያስተነትኑ ጌታችን ሆይ! ይህን በከንቱ አልፈጠርከውም ጥራት ይገባህ ከእሳትም ቅጣት ጠብቀን የሚሉ ናቸው::”

(ቅዱስ ቁርዐን 3:190-191)

በላይኛው አናቅጽ ላይ፣ አላህ በደንብ ተገልጾልናል፣ በመጀመሪያም ቀልባችንን ወደ ራሳችን በመሰብሰብ ስለአፈጣጠራችን እናስባለን:: የሰው ልጅ ልዩ ቅርጽ፣ የሰወች የተለያየ አመለካከት:: ቀልባችንን እስከ ጀነት ድረስ ይስባል:: የቀን እና የሌሊት መፈራረቅ:: ሰማይ፣ ክዋክብት፣ መላው ጠፈር . . . እናም ይህ ሁሉ ያለምክንያት እንዳልተፈጠረ ይነግረናል! ምክንያቱም የእያንዳንዱን አሰራር ስትመለከቱ፣ አሰራሩ እጅግ ጥንቅቅ ያለና ሀያል መሆኑን እንገነዘባለን:: እናም የሆነ እጅግ ሀያልና እጅግ ጥንቅቅ ያለ ከአዕምሮ በላይና ከምናስበው እጅግ የላቀ ይሆንብናል::

ለምሳሌ፣ አስር እምነበረድ ወስዳችሁ ከአንድ እስከ አስር ቁጥር ስጡት:: እናም ሁሉም የተለያዩ ቀለሞች ናቸው:: እና በቦርሳ ከትታችሁ አማትቱት:: በመቀጠል፣ አይናችሁን ጨፍኑና፣ ወደ ቦርሳው ደርሳችሁ “በቅደም ተከተል፣ ቁጥር አንድ እምነበረድን አውጡ፣ በመቀጠል ቁጥር ሁለት እምነበረድን አውጡ፣ በመቀጠል ቁጥር ሶስትን እምነበረድ አውጡ” ብትባሉ፤ እነዛን እምነበረዶች በቅደም ተከተል የማውጣት ዕድሉ ስንት ነው? ዕድሉ ስንት እንደሆነ ታውቃላችሁ? ሃያ ስድስት ሚሊዮን ለ አንድ! ስለዚህ በቢግ ባንግ ምድርንና ጀነትን እንደተገኙ ከትተን ብንመለከታቸው? የዚህ እድል ምን ይሆናል?

ውድ የተከበራችሁ እንግዶቼ:- ራሳችንን አንድ ተጨማሪ ጥያቄ መጠየቅ ያስፈልገናል. . . ድልድይ ባየን ጊዜ፣ ህንጻ ወይም አውቶሞቢል ባየን ጊዜ ወዲያው ወደ አዕምሯችን የሚመጣው ያንን የገነባው ካምፓኒ ነው:: አይሮፕላን ባየን ጊዜ፣ ሮኬት፣ ሳተላይት ወይም ግዙፍ መርከብ ባየን ጊዜ ምን ያህል አስደናቂ እንደሆነ እናስባለን:: የኑዩክለር ሀይል ማመንጫ፣ የጠፈር ምርምር ጣቢያ፣ ሁሉም ነገር የተሟላለት የአለም አቀፍ አየር መንገድ፣ እንዲሁም ደግሞ በዚህች ሀገር የሚገኙትን ሌሎች ግንባታወችን በምንመለከት ሰዐት:- ባለው የምህንድስና ልህቀት ላይ እጅግ ትገረማላችሁ::

ግን፣ እነዚህ ሁሉ በሰው እጅ የተሰሩ ናቸው:: ስለ ውስብስቡና ስለ ምርጡ የሰው አካል አወቃቀር ስርዐትስ? አስቡት! ስለ አዕምሮ አስቡ_ እንዴት እንደሚያስብ፣ እንዴት እንደሚሰራ፣ እንዴት እንደሚያጠና፣ መረጃ እንደሚያከማች፣ መረጃ እንደሚፈልግ፣ በሰከንድ አንድ ሚሊዮነኛ መረጃን የሚለይና የሚመድብ! አዕምሮ ይህን ሁሉ ያለማቋረጥ ያደርጋል:: ለአፍታ ያህል ስለ አዕምሮ አስቡ:: ይህ አዕምሮ ነው አውቶሞቢልን የሰራ፣ ሮኬትን፣ መርከብን፣ ጀልባን ሌሎችንም የሰራ:: ስለ አዕምሮ አስቡና አዕምሮን ስለ ሰራው አስቡ:: ስለ ልብ አስቡ፣ ያለማቋረጥ ለ ስልሳ እና ለ ሰባ አመት ደም ሲረጭ የሚኖር:- በመላው አካል ሲቀበልና ሲረጭ፣ ይህንንም ፍጹም የማይዋዥቅ ሂደት በሰውየው እድሜ ልክ ሲያስቀጥል:: አስቡት! ስለ ኩላሊትም አስቡ :- ምን አይነት ስራ ይሰራሉ? የሰውነት የማጣሪያ መሳሪያ፣ በመቶወች የሚሆኑ የኬሚካል ምርመራዎችን በአንድ ጊዜ የሚያከናውን፣ እንዲሁም የደማችንን መርዛማነት የሚቆጣጠር:: ይህን ሁሉ በራሱ የሚከውን:: ስለ አይናችሁ አስቡ:- የሰው ካሜራ ትኩረትን በራሱ የሚያስተካክል፣ የሚተረጉም፣ የሚገመግም፣ እናም ቀለም በራሱ የሚያክል:: ብርሀንንም ሆነ ርቀትን በተፈጥሮ የሚያስተካክል እና የሚቀበል:- ይህን ሁሉ በራሱ የሚፈጽም:: አስቡት:- ማን እንደፈጠረው? ማን የሁሉ አለቃ እንደሆነ? ማን እንዳቀደው? ማን እንደሚያስተካክለው? የሰው ልጅ :- በራሳቸው? አይሆንም . . . በፍጹም አይሆንምም::

ስለዚህ ሁሉ ጠፈር እና ሁለንታስ? አስቡት:: ምድር በጸሀይ ምህዋር ውስጥ ያለች አንዲት ፕላኔት ናት:: እና የኛ የጸሀይ ምህዋር ደግሞ በሚልክ ዌይ ውስጥ ያለ አንድ ስርዐት ነው:: እና ሚልክ ዌይ ደግሞ በጋላክሲ ውስጥ አንዱ ነው:: እንዲሁ እንደ ሚልክ ዌይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጋላክሲዎች ይገኛሉ:: ስለዛ አስቡ:: እናም ሁሉም በስርዐት ስለመሆኑ:: ሁሉም ፍጽም እንቅጯን ነው:: እርስ በእርሱም አይጋጭም፤ እርስ በእርሱም አይጣላም:: በተወሰነላቸው ምህዋር ውስጥ አብረው ይዋኛሉ:: ይህንን እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ሰወች አድርገው ይሆን? እንዲሁስ ደግሞ ይህንን ፍጹም ትክክለኛ ሂደት ሰወች ያስኬዱት ይሆን? አይሆንም፣ ሰው ፍጹም አይቻለውም::

ስለ ውቅያኖስ አስቡ፣ ስለ አሳ፣ ስለ ነፍሳት፣ ስለ አዕዋፋት፣ ስለ እጽዋት፣ ስለ ባክቴሪያ፣ ስለ ኬሚካል ንጥረ ነገሮች ስላልተገኙት እና ፍጹም በተወሳሰበ መሳሪያ እንኳ ሊገኙ ስለማይችሉት:: ግን፣ እያንዳንዷ የሚከተሉት የራሳቸው የሆነ ህግ አላቸው:: ሁሉም በአንድነት፣ በመመጣጠን፣ በተስማሞት፣ በልዩነት፣ በአሰራር፣ በመጠጋገን፣ በመተግበር፣ እናም በእልፍ ቁጥር ይከወናል:- ታዲያ ይሁሉ በአጋጣሚ የሆነ ነው? እንዲሁም ደግሞ፣ ይህ ሁሉ ሁልግዜም በፍጹም ያለመዋዠቅ የሆነው በአጋጣሚ ይሆን? እንዲሁስ ራሳቸውን እያባዙና እየጠገኑ ያሉት በአጋጣሚ ይሆን? አይደለም፣ በፍጹም ሊሆንም አይችልም::

እንዲህ ብሎ ማሰብ ቂል መሆን እና ከትክክለኛ አስተሳሰብ ያፈነገጠ መሆን ነው:: ሲጀመር እንዲሁ የመጣ ቢሆን እንኳ፣ ከሰው ልጅ አዕምሮ በላይ መሆኑን ያመላክተናል:: ሁላችንምም በዛ እንስማማለን:: ለዚህ ሁሉ ምስጋናና ክብር የሚገባ ለዘላለም ሀያል ለሆነው ለአምላክ ነው:: አምላካችን ይህን ሁሉ ፈጠረ፣ ይህን ሁሉ ለማስቀጠልም ሀላፊነቱ የእርሱ ነው:: ስለሆነም፣ አምላካችን በብቸኝነት ምስጋናና ክብር የሚገባው ነው::

ለእያንዳንዳችሁ መቶ ብር ብሰጥ፣ ያለምንም ምክንያት፣ እዚህ ስለመጣችሁ፣ ቢያንስ ቢያንስ “አመሰግናለሁ” ትላላችሁ:: ይሁን እንጂ፣ ለአይናችን፣ ለኩላሊታችን፣ ለአዕምሯችን፣ ለነፍሳችን፣ ለትንፋሻችን፣ ለልጆቻችን ምን እንላለን? ስለዚህ ምን ብለናል? ማንስ ይህን ሁሉ አድርጎልናል? ከምስጋናና ከሙገሳስ በላይ አይገባውም ነበርን? የእናንተ አምልኮና እውቅና የሚገባው አልነበረምን? ወንድሞቼና እህቶቼ፣ የዚህ ህይወታችን አላማና ትርጉም በ ቅርፊቱ ውስጥ እንዳለ የለውዝ ፍሬ ነው::

አላህም በቁርዐን እንዲህ ብሏል:

“ጋኔንንና ሰውንም ሊገዙልኝ እንጂ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም”

(ቅዱስ ቁርዐን 51:56)

ይህ ነው የዘላለም አምላክ የተናገረው:: ስለዚህ የኛ የመኖራችን ትርጉም ፈጣሪያችንን ማወቅ እና ለፈጣሪያችን አመስጋኝ መሆን ነው:: ፈጣሪያችንን ለማምለክ:: ራሳችንን ለፈጣሪ አስልፎ መስጠት፣ ያስቀመጠልንን ትዕዛዛት ማክበር:: በለውዝ ቅርፊት ውስጥ ማለት ማምለክ ማለት ነው:: ይህ ነው የህይወታችን ትርጉም:: እና ምንም እናድርግ ምንም በ አምልኮ ሂደት የመብላታችን፣ የመጠጣታችን፣ የመልበሳችን፣ የመስራታችን፣ በህይወት ያለን ደስታ እና በሞት ያለ . . ሁሉም ተከታይ ውጤት ነው:: ሁላችንም እናመልከው ዘንድ ተፈጥረናል :- ይህ ነው የህይወታችን ትርጉም:: የሳይንስ ወይም የተንታኝ ሰው ቢሆን እንኳ በዚህ የመኖር ትርጉማችን እንደሚስማማ አምናለሁ:: ምናልባት የሆነ ስውር ትርጉም በውስጡ ሊኖር ይችላል፣ ግን ያ የሚሆነው በራሳቸው እና በዘላለም አምላክ መካከል ሲያስማሙት ብቻ ነው::

አሁን ወደ ሁለተኛው ግማሽ ርዕስ እንግባ:: ስለ እስላም ምን ታውቃለህ? ስለ እስላም የሰማሀውን አይደለም:: ያየሀውን የሙስሊሞች ድርጊትም አይደለም፣ ምክንያቱም በእስላምና በሙስሊም ዘንድ ልዩነት አለ:: በአባት እና በሰው መካከል ልዩነት እንዳለው:: ልጅ ያለው ሰው አባት ነው፣ ግን አባት መሆን ሃላፊነትን መሸከም ነው:: ያ ሰው ያሉበትን ሃላፊነቶች ካልተወጣ፣ በእርግጥም ጥሩ አባት አይደለም:: እስላም አገዛዝ እና ስርዐት ነው:: ሙስሊሙ ለመገዛት እና ለስርዐት የማይሆን ከሆነ፣ ጥሩ ሙስሊም አይደለም:: ስለዚህ እስላምን ከሙስሊሞች ጋር ማነጻጸር አይቻልም::

ብዙውን ጊዜ “እስላም” እና “ሙስሊም” የሚሉ ቃላትን በብዛት እንሰማለን:: ስለ እስላምና ስለ ሙስሊምም በመጽሄቶች፣ በኮሌጅና በዩኒቨርሲቲ መጽሀፍት እናነባለን:: ብዙ የተሳሳቱ፣ አሳሳች፣ ሆን ተብሎ የተዘጋጀ መጥፎ መረጃወችን ከሚዲያ እናያለን እንሰማለን:: እና እነዚህ መጥፎ መረጃወች እና መጥፎ ውክልናወች የሚስተጋቡት በራሳቸው በሙስሊሞች መሆኑ የማልክደው ሀቅ ነው:: እንዲህም ሆኖ ከእያንዳንዱ አምስት ሰወች ውስጥ አንዱ ሙስሊም ነው! ይህን ስታስቲክ እናንተው ራሳችሁ ከኢንሳይክሎፒዲያ ወይም ከ አልማናክ ወይም ከሌላ ምንጭ ማረጋገጥ ትችላላችሁ:: እንዲህ ከአለማችን ከአምስቱ አንዱ ሙስሊም ከሆነ፣ እንዴት ስለ እስላም የሆነ ነገር አናውቅም? ስለ እስላም አንዳንድ እውነታወች:: ከአለማችን ከአምስቱ አንዱ ቻይናዊ እንደሆነ ብነግራችሁ፣ የእወነትም . . . አንድ ቢሊየን ቻይናዊ በአለም ይገኛል፣ ከአምስቱ አንዱ ቻይናዊ ነው! እናም ከጂኦግራፊካል፣ ከማህበራዊ፣ ከኢኮኖሚያዊ፣ ከፖለቲካዊ፣ ከፊዞሎፊካል፣ ከታሪካዊ የቻይና እና የቻይናዊያን ሁነቶች አኳያ ስለእነሱ አወቀን ሳለ፣ እንዴት ስለ እስላም ሳናውቅ ቀረን?

በአለም ላይ ያሉ ሀገሮችን በሙሉ ወደ አንድ አለም አቀፋዊ አንድነት ምን ሊያመጣቸው ይችላል? በየመን የሚገኘውን ወንድሜን ወይም የምትገኘውን እህቴን ወንድሜ እና እህቴ ሊያደርግ የሚችል፣ እና እኔ ከአሜሪካ፣ እና ይህን ኤርትራዊ ወንድም ወንድሜ ወይም እህቴ ሊያደርግ የሚችል:: እና ሌላ ወንድም ከኢንዶኔዥያ ወንድሜ የሚያደርገው:: እንዲሁ ከ አፍሪካ ወንድም የሚሆነኝ:: እና ሌላም ደግሞ ከታይላንድ ወንድሜ የሚሆን፣ ከ ጣልያን፣ ከግሪክ፣ ከፖላንድ፣ ከኦስትሪያ፣ ከኮሎምቢያ፣ ከቦሊቪያ፣ ከኮስታሪካ፣ ከቻይና፣ ከስፔን፣ ከሩስያ፣ እንዲሁ ከሌሎችም . . . ምንድን ወንድሞቼና እህቶቼ ያደርጋቸዋል!? እኛ ከተለያየ ባህልና የስነ አዕምሮ ማንነት ቢኖረንም! ስለ እስላም ምንድን ነው ወዲያው ሊያላምደን የሚችል እና እንደወንድማማች የሚያስተያየን? የሰው ልጆች የሚከተሉትን የህይወትን መንገድ እንዳይገነዘቡት ያደረገው ትክክለኛው አይነተኛ ጸባይ ምንድን ነው?

አንዳንድ እውነታወችን ለማቅረብ እሞክራለሁ:: ግን ከዚህ በተጨማሪ፣ ከዚህ በፊት እንደገለጽኩላችሁ፣ አዕምሯችሁን መክፈት እና ልባችሁን መስጠት ያስፈልጋችኋል:- ምክንያቱም፣ ብርጭቆን ደፍቼ ውሀ ባፈስበት፣ በፍጹም በብርጭቆው ውሀ አላገኝበትም:: ቅን እና የሚቀበል መሆን አለበት:: እውነታወች ብቻ ግንዛቤ ሊፈጥሩ አይችሉም፤ ግን የመቻቻል፣ የመልካም ምኞት፣ እንዲሁም እውነታን የመቀበል እና የመገንዘብ ችሎታወች ጥምረት ነው::

“እስላም” የሚለው ቃል ትርጉሙ መማረክ፣ ማፍራትና መከተል ማለት ነው:: ለዘላለም ለሆነው የአምላክ ህግ መማረክ፣ ማፍራትና መከተል ማለት ነው:: “አላህ” ማለት ትችላላችሁ:: “ፈጣሪ” ማለት ትችላላችሁ:: “የበላይ አምላክ” ማለት ትችላላችሁ፣ “ሀያሉ ጌታ”፣ “የሁሉም ጥበበኛ” የሚሉት ሁሉ ስሞቹ ናቸው::

ሙስሊሞች ለአምላክ አላህ የሚለውን የአረብኛ ቃል ይጠቀሙታል፣ ምክንያቱም በአረብኛ ሌላ መገለጫ የለውምና ነው:: አላህ የሚለውም ቃል ለፍጡር አይሰጥም:: ሀያል የሚለውን ቃል ለሌሎች ሰወች ለፈጠሯቸው ነገሮች ይሰጧቸዋል:: ለምሳሌ “ሀያሉ ዶላር::” “ኦ ሚስቴን እወዳታለሁ፣ እሷ ምርጧ ናት!” ወይም “እሱ ምርጡ ነው::” የለም የለም . . . “አላህ” የሚለውን ቃል የምንችለው ግን ሁሉን ለፈጠረና አስቀድመን ለገለጽነው ብቻ ነው:: ስለዚህ ከዚህ ነጥብ በመነሳት፣ “አላህ” የሚለውን ቃል እጠቀማለሁ፣ እናንተም ስለማን እያወራሁ እንዳለሁ ታውቃላችሁ::

እስላም የሚለው ቃል ስሩ “ሰላማ” ወይም ሰላም ከሚለው የመጣ ነው:: ስለዚህ፣ ሙስሊም ማለት ለዘላለማዊው አምላክ ህግ የተማረከ፣ የሚያፈራ፣ እንዲሁም የሚከተል ማለት ነው:: እናም በማፍራታቸው ሰላማቸውን እና እርጋታቸውን ያገኛሉ:: በቀጥታ ልናገኘው የምንችለውም፣ እንዲህ ባለ ትርጉም፣ የአረብኛ ቃል “እስላም” በደንብ የሚታወቁትን እና የተከበሩትን የዘላለም አምላክ መልዕክተኛ እና ነብያትን በተመሳሳይ መልኩ እንደሚገልጽ እንረዳለን:: ሁሉንም ከ አዳም፣ ኖህ፣ አብርሀም፣ ሙሴ፣ ዳዊት፣ ሰሎሞን፣ ይስሀቅ፣ እስማኤል፣ ያዕቆብ፣ መጥምቁ ዩሀንስ፣ ሱሌማን፣ እየሱስ የማርያም ልጅ፣ እና መሀመድ (ሰላም በእነርሱ ሁሉ ላይ ይሁንና) ያካትታል:: እነዚህ ሁሉ ሰወች፣ እነዚህ ነብያትና መልዕክተኞች፣ የመጡት ከአንድ የዘላለም አምላክ ነው፣ ከመልዕክቱ ጋር፣ ከማይለወጥ መልዕክት ጋር፣ ሁሉም አንድ ነገር ይላሉ _ አምላክን ተከተሉ! የዘላለም አምላክን አምልኩ እና የህይወትን ትርጉም አሟሉ እና መልካም አድርጉ፣ እና በዚያኛው ህይወታችሁ ሽልማትን ታገኛላችሁ:: ያንን ነው ሁሉም የተናገሩት! ከዚያ የበለጠ አታድርጉት! የተናገሩት ሁሉ ያ ነው፣ በየትኛውም ቋንቋ ይሁን ጊዜ፣ ከየትም ይምጡ የተናገሩት ሁሉ ያ ነው::

ቅዱስ መጽሀፍንም በጥንቃቄ ብታነቡ፣ ያለ እናንተ ትርጓሜ ሆነ ያለ ሌላ ሰው ጭማሪ ወይም ፈጠራ : መልዕክቱ ቀላል እንደሆነ እና ሁሉም ነብያት ከአንዱ እስከሌላው ያረጋገጡት እንደሆነ ትረዳላችሁ:: አንዳቸውም ነብያት “እኔ አምላክ ነኝ አምልኩኝ” አላሉም:: ባሏችሁ ቅዱስ በሚባሉት መጽሀፍቶች ሁሉ አታገኙትም በመጽሀፍ ቅዱስም ሆነ በ ቶራህ ወይም ደግሞ በሀዲስ ኪዳን ወይም ደግሞ በመዝሙረ ዳዊት በየትኛውም መጽሀፍት አታገኙትም:: በነብያት ንግግርም አታገኙትም:: ወደ ቤታችሁ ሄዳችሁ በመጽሀፍ ቅዱስ ገጾች በሙሉ ፈልጉት፣ እናም ዋስትና እቆማለሁ _ ለአንዴ እንኳ አታገኙትም:: የትም! ስለዚህ ይህ ሁሉ ከየት መጣ? ይህንን ነው ማጣራት ያለባችሁ ነገር::

በእንዲህ ባለ አገላለጽ፣ ሁሉም የአረብ ቃላት ነብያት የሰሩትን በሙሉ መግለጻቸውን እናያለን:: ሁሉም መጠው ለአምላክ ፍሬ የሚያፈሩ ነው የሆኑት ፤ የአምላክ ምርኮኛ ሆነዋል፣ የአምላክ ህዝብ ተብለዋል፤ እናም ሰወችን መልካምነትን እንዲከተሉና እንዲፈልጉ ጠይቀዋቸዋል:: የሙሴ አስርቱ ትእዛዛት _ ምን ነበር? የአብርሀም ንግግር _ ምን ነበር? የዳዊት መዝሙር _ ምን ነበር? የሰሎሞን ምሳሌ _ ምን ተናገረ? የእየሱስ ክርስቶስ ወንጌል _ ምን ተናገረ? መጥምቁ ዮሀንስ ምን ተናገረ? ይስሀቅ እና እስማኤል ምን ተናገሩ? ሙሀመድስ ምን ተናገረ? ከዚህ የበለጠ ምን አለ!

“አላህን ሀይማኖትን ለእርሱ ብቻ አጥሪዎች ቀጥተኞች ሆነው ሊገዙለት ሶላትንም አስተካክለው ሊሰግዱ ዘካንም ሊሰጡ እንጅ ያልታዘዙ ሲሆኑ (ተለያዩ ) ይህም የቀጥተኛይቱ (ሀይማኖት) ድንጋጌ ነው::”

(ቅዱስ ቁርዐን 98:5)

አላህ የተናገረው ይህን ነው:: የታዘዙትም ከአላህ በቀር እንዳያመልኩ፣ ለእርሱም የታመኑ እንዲሆኑ:: እናም ይህ ነበር ቀጥተኛውና፣ የመጀመሪያው መልዕክት::

በተመሳሳይ አባባል፣ ነብያትንም ሆነ መልዕክተኞችን ሙስሊም እንደነበሩ ማሰብ ተገቢ ነው፣ ምክንያቱም “ሙስሊም” ምንድንነው? ስለ አረብኛው አገላለጽ አታስቡ፣ እንዴት እንደምናቀርበውም አታስቡ _ ስለ መካ አታስቡ ወይም ስለ ሳዑዲ አረቢያ ወይም ደግሞ ስለ ግብጽ:: አይደለም! “ሙስሊም” ስለሚለው ቃል አስቡ:: እርሱ ራሱን ለአምላክ አሳልፎ የሰጠ፣ የዘላለም አምላክን ህግ የሚከተል፣ በዚህ ምክንያት በተፈጥሮ ወይም በሀሳባዊ ፍጭት መልኩ _ ማንኛውም ራሱን ለዘላለም አምላክ አሳልፎ የሚሰጥ ሙስሊም ነው!

ስለዚህ፣ ህጻን ልጅ አምላክ በፈቀደ ሰዐት ከእናቱ ማህጸን ሲወጣ ጀምሮ ምንድን ነው? ሙስሊም ነው:: ጸሀይ ምህዋሯን ጠብቃ ስትዞር _ ምንድን ነው? ሙስሊም ነው! ጨረቃ ጸሀይን ስትዞር _ ምንድን ነው? ሙስሊም ነው! የመሬት ስበት ህግ _ ምንድን ነው? የሙስሊም ህግ ነው! ራሱን ለዘላለም አምላክ የሚያፈራ ሙስሊም ነው! ስለዚህ፣ በፈቃደኝነት የዘላለም አምላክን ስንከተል ሙስሊም ነን! እየሱስ ክርስቶስም ሙስሊም ነበር:: የተባረከች እናቱም ሙስሊም ነበረች:: አብርሀም ሙስሊም ነበረ:: ሙሴ ሙስሊም ነበረ:: ሁሉም ነብያቶች ሙስሊም ነበሩ! ግን ወደ ህዝባቸው መጥተው ሲናገሩ በተለያየ ቋንቋ ነበር:: ነብዩ መሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) አረብኛ ተናጋሪ ነው:: እና ስለዚህ፣ በአረብኛ ቋንቋ የሚያፈራና የሚማረክ የሆነ ከሆነ ሙስሊም ነው:: ሁሉም የሀያል አምላካችን ነብያት እና መልዕክተኛች ሁሉ ወደ አለም ያመጡት መልዕክት መሰረታዊና ተመሳሳይ ነው _ “የዘላለም አምላክን አምልኩ፤ ለእርሱም ታመኑ::” ሁሉም የሚያውቃቸውን መልዕክተኞች መልዕክት ስንመረምር፣ ይህን እውነታ በቀላሉ መደምደም እንችላለን::

ግጭት የሚከሰተውም፣ በተሳሳተ ድምዳሜ፣ በፈጠራና በማጋነግ፣ በግለሰባዊና በማይረጋገጡ ትርጓሜዎች፣ በታሪክ ጽሁፍ መዘክሮች፣ በምሁራን፣ እና በግለሰቦች ውጤት ነው:: ለምሳሌ፣ እናንተም ከዚህ በፊት ልታስተውሉት የምትችሉትን ነገር ላመላክታችሁ:: እኔም ሙስሊም ከመሆኔ በፊት እንደ ክርስቲያን አስተውየው የነበረውና ያልተገነዘብኩትን:: በብሉይ ኪዳን አምላክ እንደ አንድ _ አለቃ እና ጌታ፣ የአለሙ ሁሉ ንጉስ እንደሆነ ይጠቀሳል:: ሙሴ የተሰጠው የመጀመሪያው ትእዛዝም፣ የሙታን ስዕሎችን እንዲያመልክ የማይፈቅድ፣ በገነት ላሉት በጥልቁ ባህርም ሆነ በምድር ለሚኖሩት መስገድ ፈጽሞ የሚከለክል ነው:: ሁሉም መልዕክተኞች አንድ አምላክ ብቻ እንዳለ ተናግረዋል:: በብሉይ ኪዳን ውስጥም ደግሞ ተደጋግሞ እናገኘዋለን:: በመቀጠልም፣ እንደ ድንገት አራቱን መረጃወች እናገኛለን _ አራቱ ወንጌሎችን ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስ እና ዮሀንስ ተብለው የሚጠሩትን:: ማቴዎስ ማን? ማርቆስ ማን? ሉቃስ ማን? ዮሀንስ ማን? አራት የተለያዩ ወንጌሎች በ አርባ ስምንት አመታት ልዩነት ውስጥ የተጻፉ:: አንዳቸውም ቢሆን፣ እርስ በእርሳቸው አልተጣመሩም፣ አንዳቸውም ቢሆን የ አባታቸውንም ስም አልጻፉም:: ለዚህ ወር ደሞዝዎ የኔን ስም ብቻ ጽፌ ከባንክ እንድትወስዱ ብነግራችሁ _ ያንን ቼክ ትቀበላላችሁ? የለም፣ አታደርጉትም . . . ፖሊስ ቢያስቆማችሁና ማንነታችሁን የሚገልጽ ቢጠይቃችሁ የእናንተ ስም ብቻ ያለበት መታወቂያ ወይም ፓስፖርት የሚቀበላችሁ ይመስላችኋል? በመጀመሪያ ስማችሁ ብቻስ ፓስፖርት ታገኛላችሁ? እናት እና አባታችሁ አንድ የእናንተን ስም ብቻ ይሰጧችኋል? በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥስ አንድ የራስ ስም ብቻ እንደመረጃ የሚቀበል የት ነው, እኮ የት? የትም! ከ ሀዲስ ኪዳን ውጭ::

እና እንዴት የአባት ስማቸውን እንኳ የማያውቁ በሚመስሉ አራት ሰወች የተጻፈን አራት ወንጌሎች ላይ እምነታችሁን ትመሰርታላችሁ? በመቀጠልስ፣ ከእነዚህ አራት ወንጌሎች በኋላም፣ አስራ አምስት ተጨማሪ መጽሀፍት ክርስቲያኖችን ሲገድል፣ ሲገርፍ የነበረና እየሱስን በህልሙ ማተቱን በመናገር እምነቱን በለወጠ ሰው ተጽፈዋል:: እናም የእየሱስ ሰባኪ ለመሆን በቅቷል:: ስለ ሂትለር ብነግራችሁ፣ እነዛን ሁሉ አይሁዶች ከገደላቸው በኋላ፣ እሱ ራሱ እንዲድን ቢወስንና፤ ክርስቶስን ወይም ሙሴን በማግኘቱ አይሁድ ቢሆንና፤ በቶራህ ላይ የሚታከል አስር አምስት መጽሀፍትን ቢጽፍ _ በአይሁዶች ተቀባይነት ይኖረዋል? የለም፣ ተቀባይነት አይኖረውም:: ስለዚህ እንዴት አራቱ መጽሀፍቶች የአባት ስም በሌላቸው ተጻፉ፣ እና አስራ አምስቱ ሌሎች መጽሀፍቶች ደግሞ በሌላ ሰው ተጻፉ _ ይሄኔ ነው አምላክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰው የተባለው፣ ይሄኔ ነው አምላክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሶስት ነው የተባለው፣ እናም ለመጀመሪያ ጊዜ አምላክ ልጅ የተሰጠው _ ይህ እንዴት ለክርስቲያኖች ተቀባይነት ይኖረዋል? እኮ እንዴት? አስቡበት! በዚህ ነጥብ ላይ አንከራከርም:: ብቻ እንድታስቡበት ሰጠኋችሁ እንጂ::

የነብዩ መሀመድ(ሰ.ዐ.ወ) መምጣት አዲስ ሀይማኖት አላመጣም ወይም ደግሞ አንዳንድ ሰወች በጨለምተኝነት እንደሚሉት የተለየ አይነት የአኗኗር ዘየ አላመጣም:: በተቃራኒው፣ በግል ባህርይውም ሆነ ከዘላለም አምላክ በራዕይ በተቀበለው ማንነት፤ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ከእርሱ በፊት የነበሩትን መልዕክተኞችና ነብያትን ህይወት እና መልዕክት አረጋግጧል:: ነብዩ መሀመድ(ሰ.ዐ.ወ) የተቀበለው ክቡር ውድና ቅዱስ የሆነው መጽሀፍ ቁርዐን ይባላል:: ትርጉሙም “የሚደገም የሆነ” ማለት ነው:: ምክንያቱም መሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) ቁርዐንን አልጻፈውም:: ቁርዐንን አልደረሰውም:: ማንም ቁርዕንን ይጽፍ ዘንድ ሊረዳው አልመጣም:: እና ማንም በዚህ ላይ ከእርሱ ጋር አልተጣመረም:: መልአኩ ገብርኤል ቃላቶችን ደገመለት እንጂ! የዘላለም አምላክም በልቡ እንዲይዝ ገልጾለታል:: የነብዩ መሀመድ(ሰ.ዐ.ወ) ልብም እንዲቀበል ተገልጾለት ስለነበር ቁርዐን ለነዚህ ሁሉ አመታት ያለምንም ለውጥ ሊኖረን ችሏል:: በአለም ላይ እንደነበር ያለምንም ለውጥ የተያዘ ሌላ የምታውቁት መጽሀፍ አለ? ምንም መጽሀፍ የለም . . . ቁርዐን ብቻ::

ይህን እኔ ያልኩኝ እንዳይመስላችሁ! ወደ ቤተ መጽሀፍት ሄዳችሁ ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ምን እንደሚል አንብቡ፣ ወይም የአለም ኢንሳይክሎፒዲያ፣ ወይም የአሜሪካውያን ኢንሳይክሎፒዲያ፣ ወይም ሌላ በሙስሊም ያልተጻፈ አለም አቀፋዊ ኢንሳይክሎፒዲያ ስለ እስላም፣ ስለ ቁርዐን፣ ስለ መሀመድ(ሰ.ዐ.ወ) ምን እንደሚል አንብቡ:: ሙስሊም ያልሆኑት ስለ ቁርዐን፣ ስለ እስላምና መሀመድ(ሰ.ዐ.ወ) ምን እንደሚሉ አንብቡ:: ስለሆነም እየተናገርኩ ያለሁት አለም አቀፋዊ እውቅና ያለውና ግልጽ ነው! መሀመድም(ሰ.ዐ.ወ) በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ታላቅ ሰው የነበረ ነው:: ምን እንደሚሉ አንብቡ:: ቁርዐን እጅግ አስደናቂ፣ በስነ ጽሁፍ ታሪክ ውስጥ በጣም ታላቅ የሆነ ስራ ነው! ምን እንደሚሉ አንብቡ:: የእስልምና የህይወት መንገድም ያልተወላገደ የሆነና በጋለ ስሜት ውስጥ የሚመደብ ነው! . . . ተለውጦም አያውቅም::

መሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) የተቀበለው ቅዱስ እና ክቡር የሆነው መጽሀፍ “ቁርዐን” ይባላል:: እያንዳንዳቸው ነብያትና መልዕክተኞችም ቅዱስ መጽሀፍን ተቀብለዋል:: በቁርዐን ውስጥም የእነዚህ ነብያት፣ የቅዱስ መጽሀፋቸው፣ ታሪካቸው፣ የተልዕኳቸው አስተምህሮ በታላቅ ገለጻና ዝርዝር ተጠቅሷል::

“መሀመድ ከወንዶቻችሁ የአንድም ሰው አባት አይደለም ግን የአላህ መልዕክተኛ የነቢዮች መደምደሚያ ነው አላህም በነገሩ ሁሉ አዋቂ ነው::”

(ቅዱስ ቁርዐን 33:40)

ሙስሊሞች መሀመድን አያመልኩም፣ እኛ “መሀመዳዊያን” አይደለንም:: እኛ መሀመድ የሚለውን ስም ቀይረን “መሀመዳዊያን” የማለቱ መብት የለንም:: የለም፣ ሙሴን ሲከተሉ የነበሩ ህዝቦች “ሙሴያዊያን” አልነበሩም፣ ያዕቆብን ሲከተሉ የነበሩ ህዝቦች “ያዕቆባዊያ” አልነበሩም:: ወይም አብርሀምን ሲከተሉ የነበሩ ህዝቦች “አብርሀማዊያን” አልተባሉም:: ወይም “ዳዊታዊያን” . . . የለም፣ የለም፣ የለም:: ስለዚህ እንዴት ሰወች ራሳቸውን “ክርስቲያን” ብለው ይጠራሉ? ክርስቶስ ራሱን “ክርስቲያን” ብሎ አልጠራም፣ ስለዚህ እንዴት ሰወች ራሳቸውን “ክርስቲያን” ብለው ይጠራሉ?

እየሱስ ክርስቶስ እንደተናገረው ከዘላለም አምላክ የተቀበለው ነገር ምንም ይሁን የአምላክ ቃል ነው፣ እናም የሚሰማው የሚናገረው ነው! ያደረገውም እንዲሁ ነው! ስለዚህ እንዴት እነዚህ ሰወች ራሳቸውን “ክርስቲያን” ብለው ይጠራሉ? ክርስቶስን መምሰል ይገባናል! እና ክርስቶስስ ማንን ይመስል ነበር? እርሱ የዘላለም አምላክ አገልጋይ ነበረ፤ ስለዚህ እኛም የዘላለም አምላክ አገልጋይ መሆን ይገባናል፣ በቃ ይሀው ነው!

የመጨረሻው ቅዱስ መጽሀፍ እና ራዕይ እንደሚለው፣ ቁርዐን በጣም ግልጽ እና አጭር መልዕክት አስቀምጧል፣

“ .ዛሬ ሀይማኖታችሁን ለእናንተ ሞላሁላችሁ ጸጋየንም በእናንተ ላይ ፈጸምኩ:: ለእናንተም እስላምን ከሀይማኖት በኩል ወደድኩት”::

(ቅዱስ ቁርዐን 5:3)

ስለዚህ እስላም የሚለው ቃል የመጣ ከቁርዐን ውስጥ ነው:: ምክንያቱም፣ ህንጻው ሲጠናቀቅ፣ “ቤት” ብላችሁ እንደምትጠሩት:: መኪናም ገና በመገጣጠም ላይ እያለ “አውቶሞቢል” አይደለም _ በመገጣጠም ላይ ያለ ነው! በሚጠናቀቅበት ጊዜ፣ ማረጋገጫ ይሰጠዋል፣ ሙከራ ይነዳል _ ከዚህ በኋላ ነው አውቶሞቢል የሚባለው:: እስላም በራዕይ ተሟልቶ እያለ፣ በመጽሀፍ፣ በነብዩ መሀመድም(ሰ.ዐ.ወ) ምሳሌነትም ከሆነ በኋላ “እስላም” ተባለ:: የተሟላ የህይወት አካል ሆነ::

ስለዚህ አዲሱ ነገር ቃሉ ነው . . . ተግባሩ አይደለም . . . ነብዩ አይደለም . . . የአምላክ ትእዛዝ አይደለም . . . አዲስ አምላክ አይደለም . . . አዲስ ራእይ አይደለም . . . ግን ስሙ ብቻ:: እናም ከዚህ ቀደም እንደተናገርኩት፣ ነብያት በሙሉ ምን ነበሩ? ሙስሊም ነበሩ:: ልታስታውሱት የሚገባ ሌላ ልዩነት መሀመድ፣ ከበቀደሞቹ በተለየ ለአረቦች ወይም ደግሞ ለራሱ ህዝቦች ብቻ አልመጣም:: የለም. . . ስለዚህ፣ እስላም ለአረብ የተሰጠ ሀይማኖት አይደለም:: ምንም እንኳ የአብዱላህ ልጅ፣ ነብዩ መሀመድ በአረብ ምድር በመካ ከተማ በትውልድ አረብ ሆኖ ቢወለድም፣ እስላምን ለአረቦች ብቻ አይደለም ያመጣው:: እስላምን ለመላው ህዝብ እንጂ::

ምንም እንኳ ቁርዐን የተጻፈው በአረብኛ ቋንቋ ቢሆንም፣ የመሀመድ መልዕክት ለአረቦች በልዩነት የቀረበ እንደሆነ ወይንም ደግሞ ለእነርሱ እንደተተረጎመ ሊመስለን ይችላል::

በ ቅዱስ ቁርዐን አላህ እንዲህ ብሏል፣“(መሀመድ ሆይ!) ለአለማትም እዝነት አድርገን እንጂ አልላክንህም::”

(ቅዱስ ቁርዐን 21:107)::

ነብዩ መሀመድ(ሰላም በእርሱ ላይ ይሁንና) እንዲህ ብሏል: የሰው ልጆች ሁሉ ከአዳምና ከሄዋን ናቸው፣ አረብ የሆነው አረብ ባልሆነው ላይ የበላይነት የለውም፣ አረብ ያልሆነውም አረብ በሆነው ላይ የበላይነት የለውም፤ ነጮችም በጥቁሮች ላይ የበላይነት የላቸውም ጥቁሮችም በነጮች ላይ የበላይነት የላቸውም ከመልካም ተግባር እና ከአማኒነት በስተቀር::

በእንዲህም ተግባር፣ መሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) የመጨረሻውና ከእርሱ በፊት የነበሩት ታላላቅ ነብያቶች ዘውድ ነው:: አብዛኛውም ሰው _ እንዲሁ እንደቀላል ስለዚህ መረጃ እንኳ አያውቁም::

በአቀራረቤ ላይም ቁርዐንን እንደ ድጋፍ መረጃ እየተጠቀምኩበት ስለሆነ፣ ስለ ራሱ ቁርዐን የተወሰነ መረጃ ልስጣችሁ:: በመጀመሪያ፣ ቁርዐን የመለኮት ራዕይ ውጤት እንደሆነ ያምናል:: ይህም ማለት፣ ለመሀመድ በዘላለም አምላክ አማካኝነት ለመምሪያነት የተሰጠ ነው::

አላህ እንደተናገረው፣ “ከልብ ወለድም አይናገርም::”

“እርሱ (ንግግሩ) የሚወርድ ራዕይ እንጂ ሌላ አይደለም::”

(ቅዱስ ቁርዐን 53:3-4)

መሀመድ ለራሱ አልተናገረም፣ የሱን ሀሳብ፣ የሱን ምኞት፣ ወይም የሱን ስሜታዊነት እና መንፈስ አላደረገውም:: ግን፣ ያ ሁሉ ለእርሱ በራዕይ የተገለጸለት ነው! ይህ የ አላህ ንግግር ነው:: ስለዚህ፣ የቁርዐንን ታማኝነት እንዳሳምናችሁ፣ ማረጋገጥ ያለብኝ _ አንድ፣ እንደዚህ አይነት መጽሀፍ ለመፍጠር ለሙሀመድ የማይቻል ነው:: ሁለት፣ ለሰው ልጅ ለሆነ በሙሉ እንደዚህ አይነት መጽሀፍ ለመፍጠር እንዲሁ የማይቻል እንደሆነ አረጋግጥላችኋለሁ:: እስቲ እናስበው::

ቁርዐንም እንዲህ ይላል፣

“ከዚያም በተጠበቀ መርጊያ ውስጥ የፍቶት ጠብታ አደረግነው:: ከዚያም ጠብታዋን (በአርባ ቀን) የረጋ ደም አድርገን ፈጠርን”

(ቅዱስ ቁርዐን 23:13)

“ሰውን ከረጋ ደም በፈጠረው (ጌታህ ስም)::”

(ቅዱስ ቁርዐን 96:2)

ነብዩ መሀመድ ጽንስ የሚጀምረው በእናት ማህጸን ግድግዳ ላይ የረጋ ደም በመንጠልጠል መሆኑን እንዴት አወቀ? ቴሌስኮፕ ነበረው? ሳይቶስኮፕ ነበረው? ኤክስ ሬይ ማሳያ ነበረው? ይህ ነገር የታወቀው ከአርባ ሰባት አመታት ወዲህ ብቻ ሆኖ ሳለ፣ እንዴት ይህን እውቀት ሊቀበል ቻለ::

እንዲሁ ደግሞ፣ ውቅያኖሶች በጨዋማውና በ ንጽህ ውሀ መካከል ልዩነት የሚያደርግ ገደብ መኖሩንስ እንዴት ሊያውቅ ቻለ?

“እርሱም ያ ሁለቱን ባህሮች አጎራብቶ የለቀቀ ነው ይህ ጥምን የሚቆርጥ ጣፋጭ ነው ይህም የሚመረግግ ጨው ነው በመካከላቸውም (ከመቀላቀል) መለያንና የተከለለን ክልል ያደረገ ነው::”

(ቅዱስ ቁርዐን 25:53)

እንዴት ይህን አወቀ?

“እርሱም ሌሊትንና ቀንን ጸሀይንና ጨረቃንም የፈጠረ ነው ሁሉም በፈለካቸው ውስጥ ይዋኛሉ”

(ቅዱስ ቁርዐን 21:33)

እንዴት ጸሀይ፣ ጨረቃና ሌሎች ፕላኔቶችም በታዘዘላቸው ምህዋር ውስጥ እንደሚዋኙ ሊያውቅ ቻለ? እንዴት ይህን አወቀ? እንዲሁ፣ እንዲሁ እንዴት እነዚህን ነገሮች ሊያውቅ ቻለ? እነዚህ ነገሮች የተገኙት ከ ሀያ አምስት ወይም ከ ሰላሳ አመት ወዲህ ነው:: አሁን ቅርብ ጊዜ የተገኙት ቴክኖሎጂ እና ሳይንስ፣ እንዲሁ ደግሞ ውስብስብ የሙያ ጥበቦች፣ ከ 1500 አመት በፊት የኖረው በበረሀ ያደገው ማንበብ እና መጻፍ የማይችለው ያልተማረው በግ ጠባቂ መሀመድ(ሰ.ዐ.ወ) እንዴት ይህን መሰል ነገር ሊያውቅ ቻለ? ይህን መሰል ነገር እንዴት መፍጠር ይችላል? እና ሌላ ከእርሱ ጋር የኖረ ፣ በኋላ ወይም በፊት እንዴት በቅርብ ጊዜ የተገኘን ነገር መፍጠር ይችላል:: ይህ የማይቻል ነው!! እንዴት ከአረባዊያን ምድር ያልወጣ፣ መርከብ ላይ እንኳ ተሳፍሮ የማያውቅ ሰው ከ1500 አመታት በፊት የኖረ _ እንዴት አሁን በቅርቡ በሀያኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ የተገኘን ነገር፣ ይህን በመሰለ አስደናቂ እና ግልጽ በሆነ አገላለጽ ማድረግ ይቻለዋል?

ደግሞስ፣ ይህ በቂ ካልሆነ፣ ቁርዐን መቶ አስራ አራት ምዕራፎች፣ ስድስት ሺህ ቁጥሮች እንዳሉት ብጠቅስስ:: እና እነዚህን ሁሉ ማስታወስ ይችሉ የነበሩ በመቶወች የሚቆጠሩ ሰወች በነብዩ መሀመድ(ሰ.ዐ.ወ) ጊዜ ነበሩ:: ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ይህ የተለየ አዕምሮ ባለቤት ይሆን? ወይንስ ወንጌልን በሙሉ ማስታወስ የሚችል አለ – አንድስ እንኳ? ቶራህን ማስታወስ የሚችል ሰው አለ፣ መዝሙረ ዳዊትን፣ ብሉይ ኪዳንንና አዲስ ኪዳንን? ማንም ይህን ሊያደርግ አልቻለም:: ጳጳሱም ቢሆን::

ግን መላውን የመጽሀፍ አካል ማስታወስ የሚችሉ በሚሊየን የሚሆኑ ሙስሊሞች አሉ:: ይህም የሁሉም ሙስሊም ምኞት ነው:: የጥቂቶች አይደለም _ የሁሉም እንጂ! በህይወታችሁ አጋጣሚ መላውን መጽሀፍ ቅዱስ ማስታወስ የሚችሉ ስንት ክርስቲያኖች አጋጥሟችኋል? ምንም:: መላውን መጽሀፍ ቅዱስ ማስታወስ የሚችል አንድስ እንኳ ክርስቲያን አላገኛችሁም፣ ምክንያቱም መላው መጽሀፍ ቅዱስ እንኳ ምን እንደሆነ የሚያውቅ ክርስቲያን አግኝታችሁ ስለማታውቁ ነው:: ለምን ይህ ሆነ? ምክንያቱም፣ መጽሀፍ ቅዱስ ከ ሰባት መቶ በላይ ክፍሎች ያሉት፣ ወደ ሰላሳ ዘጠኝ የሚሆኑ የተለያዩ የመጽሀፍ ቅዱስ አይነቶች ያሉት_ ከተለያዩ መጽሀፍትና ከተለያዩ አይነቶች ጋር:: የሚለያዩ ቁጥሮች እና ምዕራፎች ስላሉት:: ስለማይስማሙም፣ ስለዚህ የማይስማሙበት ነገርን እንኳ እንዴት ሊያስታውሱት ይችላሉ::

ይህ ስለ ቁርዐን ትንሹ እውነታ ነው:: ቁርዐን ባለፉት አስራ አምስት ክፍለ ዘመናት በአለም አቀፍ ደረጃ ትንሽ እንኳ ለውጥ ሳይደረግበት ተጠብቆ ያለ ነው:: ይህንንም እንደ መውቀስ እየተናገርኩ አይደለም:: እኔ ክርስቲያን የነበርኩ ሰው ነኝ:: እነዚህን ነገሮች በራሴው ጥልቅ ምርመራ ያገኘኋቸው ሰው ነኝ:: ይህንንም መረጃ ለእናንተው በማጋራት የምትመለከቱበት መንገድ ድንጋይ በመፈንቀል እራሳችሁ እንድትታዘቡት የሚያደርግ ሰው ነኝ:: እናም ፍርዱ ለእናንተው ነው!

እስቲ ዝም ብላችሁ ይህ ሁሉ እውነት እንደሆነ አስቡ:: ይህ መጽሀፍ የእውነትም ታላቅ እንደሆነ ትስማማላችሁ? ለመናገር ያህል እንኳ ልዩ እንደሆነስ? ይህን ያህልስ እውነተኛ ትሆናላችሁ? በርግጥም ትሆናላችሁ፣ በውስጣችሁም እውነተኝነት ካላችሁ ወደዛ ድምዳሜ ትመጣላችሁ:: ብዙዎች ሙስሊም ያልሆኑት ወደዚህ ድምዳሜ መጥተዋል:: ለምሳሌ ጥቂቶችን ለመጥቀስ ያክል ቤንጃሚን ፍራንክሊን፣ ቶማስ ጀፈርሰን፣ ናፖሊዮን ቦናፓርቴና ዊንስተን ቸርችል ይጠቀሳሉ:: ሌሎች ብዙወችንና መቀጠል እችላለሁ:: ወደ ተመሳሳይ ድምዳሜ መጥተዋል:: በግልጽ እስልምናን ይቀበሉ ወይም አይቀበሉ:: ወደዛ ድምዳሜ ደርሰዋል _ በስነ ጽሁፍ ውስጥ እንደ ቁርዐን ታላቅ የሆነ መጽሀፍ የለም፣ የብልሀት ምንጭ እና የድህነት መንገድ::

አሁን ስለ ቁርዐን ትክክለኝነት አብራርተናል፣ ስለዚህ ወደ ሌላ ጉዳይ እንግባ: የቁርዐን መሰረታዊ ርዕሰ ጉዳዮች:: የአንድ የበላይ የዘላለም አምላክነት፣ ስሙን፣ አመጣጡን፣ የዘላለም አምላክ እና የፍጥረቱ ግንኙነት፣ እና የሰው ልጅ እንዴት ግንኙነቱን ማስኬድ አለበት የሚሉትን ያካትታል:: የነብያት እና የመልዕክተኞች የህይወታቸው፣ የመልዕክታቸው፣ እንዲሁም አጠቃላይ ተልዕኳቸው መቀጠል:: የመጨረሻና የነብያት እና የመልዕክተኞች መደምደሚያ ማህተም የሆነውን መሀመድ(ሰ.ዐ.ወ) መከተል:: የሰው ልጆችን የዚህን አለም አጭርነት ማስተዋስ እና ከዚህ ህይወት በኋላ ዘላለማዊ የሆነውን ህይወት እንዲሹ መጥራት:: ከዚህ ህይወት በኋላ ማለት ከዚህ በኋላ:: ከዚህ በኋላ ይህን ቦታ ትለቁና ወደ የሆነ ቦታ ትሄዳላችሁ፤ ይህ ማለት ዛሬ አይደለም:: ግን ከሞታችሁ በኋላ ምድርን ስትለቁ፣ ወደ ሆነ ቦታ ትሄዳላችህ፣ ተቀበላችሁትም ወይም አትወቁትም ወደዛ ትሄዳላችሁ፣ እናም ሃላፊነት አለባችሁ፣ ምክንያቱም ተነግራችኋል _ ባትሰሙት እንኳ:: ምክንያቱም የህይወታችን አላማ እዚህ ያለምንም ውጤት መቀመጥ አይደለም:: እያንዳንዱ መንስኤ ውጤት አለው! ወደዚህ ህይወትም የመጣችሁበት መንስኤ ወይም ምክንያት አላችሁ፣ ያ ደግሞ ውጤት ይኖረዋል:: የሆነ ውጤት እንዳለው ያስጠነቅቃል! ወደ ትምህርት ቤት ለመዋል ብቻ አትሄዱም! ለማትከፈሉበት ስራ አትሄዱም! የማትገቡበትን ቤት አትገነቡም! የማትለብሱትን ሙሉ ሱፍ ልብስ አታሰፉትም! እንደ ህጻን ሳይታደግ ጎረምሳ አይሆንም! ሽልማት ለማታገኙበት ስራ አትሰሩም! ያለመሞት ልትኖሩ አትችሉም! መቃብራችሁን ሳትጠብቁ አትሞቱም! እናም ቀብራችሁ የመጨረሻችሁ እንደሆነ አትጠብቁም:: ምክንያቱም እንደዚያ ቢሆን ኑሮ አምላክ እናንተን የፈጠራችሁ ለማይረባ ምክንያት ነበር ማለት ነው:: እና ትምህርት ቤት ባልሄዳችሁ፣ ባልሰራችሁ፣ ወይንም ምንም ባላደረጋችሁ ወይም ሚስት ባልመረጣችሁ ወይም ለማይረባው ህይወት ለልጆቻችሁ ስም ባልመረጣችሁ:: እንዴት ለአምላክ ለራሳችሁ ከምታደርጉት ያነሰ ታደርጋላችሁ?

ቁርዐንን ለየት የሚያደርገው፣ ቀደም ብለው የተጻፉ ጽሁፎቹን አረጋግጧል:: እናም፣ የእስልምና ሀይማኖትን ከመረመራችሁ በኋላ፣ ሙስሊም ለመሆን ትወስናላችሁ፣ ሀይማኖታችሁን እንደለወጣችሁም አይደለም! ሀይማኖታችሁን እየለወጣችሁም አይደለም . . . አያችሁ፣ ትንሽ ክብደት ከቀነሳችሁ፣ 500 ብር የገዛችሁትን ሱፍ አትወርውሩትም . . በርግጥም አታደርጉትም! ወደ ልብስ ሰፊም ወስዳችሁ “እባክህ ይህን ሱፍ ስለመወደው፣ ወሰድና ትንሽ አጥብብልኝ አትሉትም::” እንደዚሁም፣ በእምነታችሁ፣ በክብራችሁ፣ በምግባራችሁ፣ ለእየሱስ ክርስቶስ ፍቅራችሁ፣ በአምላክ መያያዛችሁ፣ በአምልኮታችሁ፣ በእውነተኝነታችሁ፣ ለዘላለም አምላክ ላላችሁ ትጋት – እንዲህ የምትለውጡት እና የምትወረውሩት አይደለም! ትኖሩበታላችሁ! ግን፣ እውነታው በተገለጸላችሁ ጊዜ ግን ለውጥ ታደርጋላችሁ! በቃ ይሀው ነው!

እስልምና ቀላል ነው፣ ከዘላለም አምላክ በቀር ሌላ የሚመለክ እንደለለ ምስክር መሆን:: አባታችሁ፣ አባታችሁ መሆኑን ምስክር እንድትሆኑ ብጠይቃችሁ፣ ስንቶቻችሁ “አወ አባቴ አባቴ ነው፣ ልጄ ልጄ ነው፣ ሚስቴ ሚስቴ ናት፣ እኔ እኔነቴ ነው” ትላላችሁ:: እና እንዴት የዘላለም አምላክ አንዱና ብቸኛው የዘላለም አምላክ መሆኑን፣ የዘላለም አምላክ ጌታችሁና ፈጣሪያችሁ መሆኑን ምስክር ለመሆን ትዘገያላችሁ? ለምን ይህን ለማድረግ እብሪተኛ ሆናችሁ? እናንተ አምላክ ማድረግ የማይችለውን ነገር ማድረግ ትችላላችሁ? ወይስ፣ እንዲሁ ግራ ተጋብታችኋል? ይህ ነው ራሳችሁን ልትጠይቁት የሚገባችሁ ጥያቄ::

ነገሮችን በቀጥተኛ ንቃተ ህሊናችሁ ማስቀመጥ የምትችሉበት እድሉ ቢገጥማችሁና፣ ነገሮችህ ከአምላክ ጋር ያለመወላወል ብታስቀምጡ፣ እንደዛ ማድረግ ትችላላችሁ? አምላክን ያደረጋችሁትን መልካም ስራ እንዲቀበላችሁ ማድረግ የምትችሉበት እድሉ ቢገጥማችሁ፣ ማድረግ ትችላላችሁ? ይህን ነገርስ ከመሞታችሁ በፊት የማድረግ እድሉ ቢገጥማችሁና፣ ዛሬ የምትሞቱ ከመሰላችሁ፣ አንድ አምላክ ብቻ መኖሩን ምስክር ለመሆን የምትዘገዩ ናችሁ? ዛሬውኑ የምትሞቱ ከመሰላችሁ እና ከፊታችሁ ገነት ከበስተጀርባችሁ ደግሞ ሲኦል ቢሆኑ፣ መሀመድ የመጨረሻው የአምላክ መልዕክተኛ እና የነብያት ወኪል መሆኑን ለመመስከር ትዘገያላችሁ? ስማችሁ ለአምላክ ያፈሩት በተጻፉበት መጽሀፍ ይጻፍላችሁ ዘንድ ለመታዘብ የምትዘገዩ አትሆኑም!

ግን፣ ትንሽ እድሜ የምትቆዩ ይመስላችኋል:: እናም፣ ቀን በቀን ለመጸለይ ዝግጁ አይደላችሁም! ምክንያቱም እድሚያችሁ የሚቆይ እንደሆነ ታስባላችሁ:: ግን “ትንሽ መቆየት” ምን ያህል ነው? ከስንት ጊዜ በፊት ራሳችሁ በሙሉ በጸጉር የተሸፈነ ነበር? ከስንት ጊዜ በፊት ነበር ጸጉራችሁ በሙሉ ጥቁር የነበረው? በጉልበታችሁ እና በክንዳችሁ እንዲሁም በሌሎች ቦታወች ህመምና ውጋት ሲገጥማችሁ! ከስንት ጊዜ በፊት ነበር ህጻን ሆናችሁ ያለምንም ሀሳብ ስትሮጡና ስትጫወቱ የነበረው? ከስንት ጊዜ በፊት ነበር? ትላንት ነበር! አወ:: እናም ነገ ሟች ናችሁ:: ስለዚህ ምን ያህል ጊዜ ልትጠብቁ ነው?

እስላም የዘላለም አምላክ፣ ያለምንም ቤተሰብ፣ ብቸኛ አምላክ እንደሆነ የሚመሰክር ነው:: እስላም ለነብያት ራዕይ ይገልጹ ዘንድ የተላኩ መላዕክትን ህልዉና የሚያረጋግጥ ነው:: ለነብያት መልዕክትን የሚሸከሙ:: ነፋሳትን፣ ተራሮችን፣ ውቅያኖሶችን፣ የሚቆጣጠሩና አምላክ እንዲሞት ያዘዘውን ነብስ የሚወስዱ ናቸው:: እስላም ሁሉም የዘላለም አምላክ መልዕክተኞች እና ነብያት ትክክለኛ ሰወች እንደሆኑ የሚያረጋግጥ ነው:: የተላኩት ሁሉም በዘላለም አምላክ አማካኝነት ለፍጥረታት ሁሉ የመጨረሻዋን ቀን ለማረጋገጥ የመጡ ናቸው:: እስላም ክፉንና መልካሙን የሚያረጋግጥ የዘላለም አምላክ እንደሆነ ያረጋግጣል:: በመጨረሻም፣ እስላም ከሞት በኋላ ትንሳኤ እንዳለ ያረጋገጠ ነው::

እስላም እንደ ትልቅ ቤት ነው:: እናም ሁሉም ቤት በመሰረት እና በምሰሶ ተደግፎ መሰራት አለበት:: ምሰሶ እና መሰረት:: ቤትንም ስትገነቡ በህግ ነው:: ምሰሶዎቹ ህጎች ናቸው! እና ቤታችሁን ስትገነቡ፣ ህጎችን መከተል አለባችሁ::

የእያንዳንዱ ሙስሊም መሰረታዊ ግዴታወቹም ቀላል እና በ 5 የሚጠቃለሉ ናቸው፣ እነዚህ አምስት ምሰሶ የሚባሉትም: እምነት፣ አምልኮ፣ ጾም፣ መዘከር እና ሀጂ ማድረግ ናቸው::

በእስላም ይበልጥ ጠቃሚው ህግ የፈጣሪ አንድ ብቸኝነትን ማስቀደም ነው:: ይህም ማለት፣ ቤተሰብ የለለው አምላክ ብቻ:: ከአምላክ ጋር ሌላ ምንም ነገር አለማምለክ:: ምእመናን አምላክን ያለ ምንም የቄስ ወይም የቅዱሳን አማላጅነት በቀጥታ የሚያመልኩበት:: አምላክን ማለት የሌለባችሁን ነገር ማለት እንደሌለባችሁ:: “አባት፣ ወንድ ልጅ፣ ሴት ልጅ፣ እናት፣ አጎት፣ አክስት፣ ታማኝ ሰወች አሉት” አለማለታችሁን:: አምላክን ማለት የለላባችሁን ነገር ማለት እንደሌለባችሁ:: እራሳችሁን ምስክር ስታደርጉ፣ በራሳችሁ ትፈርዳላችሁ:: የፈለጋችሁትን ፍርድ ትወስዳላችሁ:: ወይንም ከሰላምና ከገነት ትፈርዳላችሁ ወይም ራሳችሁን ለግራ መጋባት፣ ለተስፋ መቁረጥ፣ ለገሀነመ እሳት እና ለ ቅጣት ትፈርዳላችሁ:: በራሳችሁ ትፈርዳላችሁ::

ስለዚህ ራሳችሁን ጠይቁ፣ “አንድ አምላክ ብቻ እንዳለ ምስክር መሆን አለብኝ?” ይህን ጥያቄ ራሳችሁን ስትጠይቁ፣ መልሳችሁ፣ “አወ፣ ምስክር ነኝ” የሚል ይሆናል:: በመቀጠልም ይህን ጥያቄ ራሳችሁን ጠይቁ:: መሀመድ የዘላለም አምላክ መልዕክተኛ እንደሆነ ምስክር መሆን አለብኝ? “አወ፣ ምስክር እሆናለሁ::” ለዚህ ምስክር ከሆናችሁ ሙስሊም ናችሁ:: እናም የነበራችሁበትን መለወጥ አይኖርባችሁም:: እንዲሁ ምን እንደነበራችሁ በአስተሳሰባችሁና በተግባራችሁ መለወጥ አለባችሁ::

በመጨረሻም፣ ቀጥተኛና ግልጽ ጥያቄ ልጠይቃችሁ:: እየተናገርኩ ያለሁትን ተረድታችሁኛል? በተናገርኩት ነገር ከተስማማችሁና ወደ እስልምና ለመግባት ከተዘጋጃችሁ፣ ሙስሊም ለመሆን ዝግጁ ናችሁ:: ሙስሊም ለመሆን፣ በመጀመሪያ ሻህዳን “የእምነት ምስክርን” መድገም ይኖርባችኋል፤ እሱም በአምላክ አንድነት ማመን እና መሀመድን የአምላክ መልዕክተኛ አድርጎ መቀበል ነው::

لا إله إلا الله محمد رسول الله
ላ ኢላህ ኢላ አላህ፣ መሀመድ ረሱሉላህ

ከአምላክ በቀር አምላክ የለም፣ እና መሀመድ የአምላክ መልዕክተኛ ነው::

አንድ አምላክ ብቻ እንዳለ ምስክር እሆናለሁ::
መሀመድ የአላህ መልዕክተኛ እንደሆነ ምስክር እሆናለሁ::

የሚከተለውን ቪዲዩ ይመልከቱ::

አላህ ይባርከን:: አላ ህ ይምራን:: ሙስሊም ላልሆናችሁ የዚህ ጽሁፍ አንባቢያን መናገር የም ፈልገው – – ለራሳችሁ በጣም ታማኝ እንድትሆኑ ነው:: ስለአነበባችሁት ነገር አስቡ:: ይህን መረጃ ውሰዱና በደንብ አብላሉት:: ከሙስሊም ጋር ቁጭ ብላችሁ የእስልምናን ውበት ይበልጥ እንዲገልጹላችሁ አድርጉ:: ወደ ቀጣዩ ደረጃም ተሸጋገሩ!

እስልምናን ለመቀበልና ሙስሊም ለመሆን ስትዘጋጁ፣ በይፋ ሙስሊም ከመሆናችሁ በፊት ታጠቡ:: እስልምናን ተቀበሉ:: ስለ እስላም እወቁ:: እስልምናን ተግብሩ:: እናም አላህ ካቀረበላችሁ ሽልማት በደስታ ተቋደሱ፣ ምክንያቱም እምነት እንደውለታ የምትወስዱት አይደለም:: በተግባር ካላዋላችሁት፣ ጣዕሙን ታጣላችሁ:: አላህ ይምራን:: አላህ ይርዳን:: እናም በዚህ አጋጣሚ ይህን ንግግር ላደርግ በመቻሌ ክብር ይሰማኛል::

السَّلاَمُ عَلَيْكُمْ وَرَحْمَةُ اللهِ وَبَرَكَاتُهُ
አሰላሙ አሊኩም ወ ረመቱላሂ ወ በረካቱ

“ሰላም በአንተ ላይ ይሁን እንዲሁም የአላህ ምህረትና ባረኮት”

ሙስሊም ለመሆን ከፈለጋችሁና በእስልምና ላይ ተጨማሪ መረጃ ከፈለጋችሁ፣
እባካችሁ በ info@islamicbulletin.org.


ይህንን ጽሑፍ በማሽጎጫ መጽሐፍ ውስጥ ይመልከቱ / ያትሙ ፡፡

ሙስሊም መሆን የሚቻልበት መንገድ ፡፡ ቪዲዮ ፡፡